Web Content Display Web Content Display

Web Content Display Web Content Display

 

----------------

ሜሪ ኪዩሪ

 ታደለ ነጋሽ(ኢጨመባ)

መጋቢት 2010ዓ.ም

 

በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በስፖርት፣ በጦርነት፣ በምርምር፣ በአመራር፣ ወዘተ አንቱታን ያተረፉ በርካታ ስመጥር እና አርአያ የነበሩ እና  ያሉ በርካታ  እንስቶች ቢኖሩም  ከነዚህም መካከል ስለምንሰራበት ተቋም(ኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለስልጣን-ኢ.ጨ.መ.ባ) መሰረት/ምክኒያት ከሆኑት ውስጥ አንዷ የሆነችውን ማንሳት ግድ ይላል፡፡

ስለ ጨረራ ሲነሳ ስሟ በእለት ከለት ስራችን ከጨረራ ልኬት ስራዎቻችን ጋር አያይዘን እናነሳዋለን፡፡

አዎን ሜሪ ኪዩሪ!

እ.ኤ.አ. ከ1867 – 1934 የኖረችው በትውልድ ፖላንዳዊት ነገር ግን በዜግነት ፈረንሳዊት የነበረችው የኬሚስትሪ እና የፊዚክስ ሊቋ ሜሪ ኪዩሪ ከባለቤቷ ፔሪ ኪዩሪ ጋር በመሆን የ2 ጊዜ የኖቤል ሽልማትን የተቀዳጀች ሲሆን መሰረታቸውም የራጅ ጨረራ  መገኘትን ካስተዋወቀው ዊልሄልም ሮንትገን እና የጨረራ መፍለቅን ከዩራኒየም ጨው ንጥረ ነገር ካገኘው ከሄነሪ ቤኩዌረል ነበር፡፡  ቶሪየም ከተባለውም የዩራኒየም ዝርያ ጨረራ እንደሚመነጭ እንዲሁም በተጨማሪም የዩራኒየምና ራዲየም ምንጭ ከሆነ ማዕድንም ከፍተኛ ጨረራ መውጣቱን ለአለም ገሀድ አውጥታለች፡፡

በመቀጠልም ፖሎኒየም እና ራዲየም የተባሉ ጨረራ አፍላቂ ንጥረ ነገሮችን በምርምር አገኘች፡፡ ጨረራውንም ለህክምና ዘርፍ እንዲውል አደረገች፡፡

ሜሪ ኪዩሪ በአንደኛው አለም ጦርነት ላይ  ራጅ መሳሪያዎችን አምቡላንስ ላይ በማድረግ እስከ ጦር ግንባር ድረስ በመሳተፍ የጨረራን ጥቅም አገልግሎት ላይ እንዲውል ከማድረጓም ባሻገር ለህክምና ባለሙያዎች ስለአጠቃቀሙ ስልጠና  ትሰጥም ነበር፡፡

እንደ ኤ.አ በ1920ዎቹ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ ሄደ፡፡ በወቅቱ ከምርምሯ ጋር በተያያዘ አደጋ ያድርስ አያድርስ ምንም ባልታወቀበት ሁኔታ ለጨረራ ተጋልጣ በመኖሯ ለተደጋጋሚ የአይን ሞራ ቀዶ ጥገና ከመዳረጓም ባሻገር በደም ካንሰር አማካይነት ስትሰቃይ ቆይታ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 4 ቀን 1934 ይህቺን አለም ተሰናብታለች፡፡

ኪዩሪ እና ባለቤቷ አብዛኛውን ኋላቀር በሆነ ሁኔታ ምርምሮቻቸውን ሲያከናውኑ ቢኖሩም የፈጠራ ግኝቶቻቸውን ሌሎች ወጣቶችና አዳዲስ ተመራማሪዎች በነጻ እንዲጠቀሙበት በማሰብ ለግኝቶቻቸው የባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው ሲጠየቁ አሻፈረን ያሉ ጀግኖች አርአያ ነበሩ፡፡ የተሰጣቸውን የኖቤል ሽልማትና ሌሎች የገንዘብ ስጦታዎቻቸውንም ለቀጣይ ምርምሮች እንዲውሉ ለግሰዋል፡፡

ሜሪ ኪዩሪ ከራዲየም በሚወጣ  ጨረራ  አማካይነት ህክምና መስጠት መቻሉን በተለያዩ አገራት በማስተዋወቅ ዝናዋንም ተጠቅማበታለች፡፡ ከስራዎቿ ሁሉ የላቀውና  የህይወት ዋጋ ያስከፈላትም የምርምሯ ውጤት የሆነው እና ዛሬ አለም በሰፊው አገልግሎት እየሰጠበት የሚገኘው የካንሰር በሽታን በጨረራ  ማከም  ይገኝበታል፡፡

የሁለተኛው አለም ጦርነት ማሳረጊያ ላይ ጨረራ በሰው ልጆች እና በአካባቢ ላይ የሚያስከትለው ጥፋት እና ውድመት ከተለየ እና ከታወቀ በርካታ አመታት በኋላ ዓለምአቀፍ መርሆዎች ተዘጋጅተውለት የጨረራ መከላከል ስራ በመላው አለም በየአገራቱ ተጀመረ፡፡

ለጨረራ መስዋዕቷ ሜሪ ኪዩሪ ክብር ይሁን!!!

---------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ወይ ጨረራ!

ክፍል ሦስት

አዘጋጅ ታደለ ነ. (ኢጨመባ)

የጉያና(ብራዚል) ጨረራ አደጋ

ከብረታብረት ሰብሳቢው ሰራተኞች ውስጥ የአንደኛው ሚስት አብዛኛው የቤተሰብ አባላቱን የጎዳውን መንስዔ ለማሳወቅ ቁሱን በመያዝ ወደ ሀኪም ዘንድ ሄደች፡፡ የዚያኑ እለት የብረታ ብረት ገዥው ባለቤትም ትታመማለች፡፡ እሷም በጨረራ አመንጭው ዱቄት በተበከለችው እናቷ እንክብካቤ ይደረግላታል፡፡ መስከረም 23 ሁለት የብረታብረት ሰብሳቢው ሰራተኞች የጨረራ አመንጭ መሳሪያውን አካል ሲፈታቱ ለከፍተኛ ጨረራ ተጋልጠዋል፡፡ በመስከረም 24 ደግሞ የብረታብረት ሰብሳቢው ወንድም የተወሰነውን አካል ወደ ቤቱ በመውሰድ እና በመመገቢያ ጠረጴዛ ላይ በማስቀመጥ በሚመገቡበት ሰዓት በርካታ የቤተሰቡ አባላት ለጨረራ ሲጋለጡ የ6 ዓመት እድሜ ያላት ልጁ በአንድ እጇ ምግብ እየበላች በአንድ እጇ ቁሱን ታገላብጥ ነበር፡፡

መስከረም 25 ብረታ ብረት ገዥው ተፈታትቶ ከነበረው መሳሪያ የተወሰነ ክፍል ለሌላ ብረታብረት ሰብሳቢ ሸጠለት፡፡ በዚህ ሁኔታ በርካታ ሰዎች ሲታመሙ መስከረም 28 የብረታ ብረት ሰብሳቢው ሚስት ቤተሰቧ የተጎዳበትን ምክኒያት ለህክምና ባለሙያዎች ለማሳወቅ ቁርጥራጭ ብረቶችን ከሁለተኛው ብረታብረት ገዥ ላይ በመውሰድ በህዝብ መጓጓዣ በመጠቀም ከህክምና ክሊኒክ በመግባት በሀኪሙ ጠረጴዛ ላይ ታስቀምጠዋለች፡፡ በርካታ ዶክተሮች የሀሩር በሽታ ነው ብለው ሲገምቱ አንዱ ሀኪም ግን ይህ ጉዳይ ከጨረራ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጥርጣሬውን ገለጸ፡፡

መስከረም 29 ጠዋት ጉዳዩ ለሜዲካል ፊዚክስ ባለሙያ በስልክ ተነግሮት ዘግይቶ ቢደርስም የጨረራ ልኬት ስራ ሲያከናውን ያገኘው ውጤት አጠራጥሮት ለእሳት አደጋ ሰራተኞች ቁርጥራጮችን ወደ ወንዝ እንዳይጨምሯቸው አሳወቀ፡፡

በዚያኑ ዕለት ከሰዓት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለስልጣናት ተገለጸ፡፡ ወዲያውም በተበተነው የጨረራ ቁስ የተበከሉትን አካባቢዎች የመለየት ስራ እንዲሁም በተበተነው የጨረራ ቁስ የተጋለጡና የተጎዱ ሰዎችን በከተማው በሚገኝ ስታዲየም ውስጥ በማሰባሰብ ለ112800 ገደማ ሰዎች መበከል አለመበከላቸውን ለመለየት ፍተሻ የተደረገላቸው ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 23 ሰዎች ሆስፒታል እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

ከነዚህም ውስጥ የተወሰኑት ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሪዮ ዴጄኔሮ ሲላኩ ሌሎቹ እዚያው በሚገኝ አጠቃላይ ሆስፒታል እንዲታከሙ ተደረገ፡፡ ከፍተኛ ጨረራ ወስደው የነበሩት የብረት ሰብሳቢው ሚስትና የ6ዓመት ልጁ ጥቅምት 23 ሲሞቱ ሁለቱ ሰራተኞች ደግሞ ጥቅምት 27 እና 28 በተከታታይ ሞቱ፡፡ ጥቂት አመታት በህክምና ሲረዳ ቢቆይም ከጨረራ መጋለጡ ጋር በተያያዘ ጉበቱ ስራ በማቆሙ ብረታ ብረት ሰብሳቢውም ሞተ፡፡

ባጠቃላይ ከጨረራ መጋለጡ ጋር በተያያዘ 5 ሰዎች ሲሞቱ 20 ሰዎች ደግሞ ለአጥንት ውስጥ መቅኒ እጥረት፣ ለጨረራ ህመም(Radiation Sickness)፣ ለጭንቀትና ብስጩነት የመሳሰሉት ችግሮች ተዳርገዋል፡፡

ብክለቱ በተከሰተበት የከተማው ክፍል የሚገኘው የላይኛው የአፈር አካልም ተጠርጎ እንዲነሳ እንዲሁም በርካታ ቤቶች እንዲፈርሱ እና ፍርስራሾቹም ተሰብስበው ሰው፣ አፈር እና ውሀን እንዳይበክል በተለየ ቦታ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡

ይህን ያህል ቀውስ ያስከተለው እና ከአሮጌው ክሊኒክ ውስጥ ከነበረው ራዲዮቴራፒ መሳሪያ ውስጥ ተፈልቅቆ ወጥቶ የተበተነው የጨረራ አመንጭ ቁስ አይነት ሲዝየም ክሎራይድ (CsCl) በዱቄት መልክ ሲሆን መጠኑም 93 ግራም እና ተቀምጦበት የነበረው የሲሊንደር ቅርጽ ያለው መያዣም ቁመቱ 5.1 ሳንቲሜትር እና ዲያሜትሩ 4.8ሳንቲሜትር እንዲሁም ችግሩ በተከሰተበት ወቅት የጨረራ ማፍለቅ ችሎታው 50.9ቴራ ቤኩየረል(50.9TBq) ወይም 1376ኪዩሪ(1376Ci) ነበር፡፡ (ስለ ቤኩየረል እናኪዩሪ ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን)

ለዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂዎች የነበሩት የራዲዮቴራፒ መሳሪያው ባለቤቶች የነበሩት ሀኪሞች እንዲሁም የሀገሪቱ ብሄራዊ የኑክሌር እና ጨረራ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ፍርድ ቤት እንዲቀጡ አደርጓል፡፡

ለመሆኑ የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎችን ተጠቃሚ ተቋማት፣ ተቆጣጣሪ ተቋማት፣ ከመሳሪያዎቹ ጋር የሚሰሩ ባለሙያዎችና ህብረተሰቡ ግንዛቤያቸው እስከምን ድረስ ይሆን?

 

 

 

ወይ ጨረራ!

ክፍል ሁለት

አዘጋጅ፡- ታደለ ነ.(ኢጨመባ)

       በዓለማችን ውስጥ ከጨረራ ጋር ተያይዞ ካጋጠሙ አደጋዎች አንዳንዶቹ

       1ኛ

ቀን፡-  እ.ኤ.አ. መጋቢት 19 ቀን 1984

ቦታ፡-  ካዛብላንካ (ሞሮኮ)

ክስተቱ፡-  ለኢንዱስትሪያል ራዲዮግራፊ የሚያገለግል ቁስ መጥፋት

ሞሮኮ አገር በምትገኝ ካዛብላንካ ከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ወዛደር ለኢንደስትሪ ራጅ ስራ አገልግሎት ከሚሰጥ መሳሪያ ውስጥ የወደቀ ኢራዲየም-192 (Ir-192) የተባለ የጨረራ የማፍለቅ አቅሙ 16.3ኪዩሪ (Activity16.3Ci) የሆነ ቁስ ወድቆ አግኝቶ ወ ቤት ይወስዳል፡፡ እቤቱም እንደደረሰ መኝታ ቤቱ ውስጥ በሚገኝ ጠረጴዛ ላይ ያስቀምጣል፡፡ ሳያነሳውም ጥቂት ሳምንታት ይቆያል፡፡ ቁሱ በሚያወጣው ጨረራ አማካይነት በ 45 ቀናት ውስጥ የተጋለጡ 4 ህጻናትና ወላጆቻቸውን ጨምሮ በቀናት የቤተሰቡ ስምንት አባላት አልቀዋል፡፡ ተጨማሪ ሶስት ሰዎችም እጅግ ከፍተኛ ለሆነ ጨረራ ተጋልጠዋል፡፡ ምርመራ እንኳ የተካሄደው ከመጀመሪያው መጋለጥ ከ 80 ቀናት በኋላ ነበር፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያንስ ወድቀው ያገኘናቸውን ቁሳቁስ ሁሉ ወደቤት መውሰድ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር እናስበው ይሆን?

       2ኛ

ቀን፡-  እ.ኤ.አ. ጥቅምት 5 ቀን 1982

ቦታ፡-  ባኩ (አዘርባጃን)

ክስተቱ፡-  ባለቤት ከሌለው ቁስ መጋለጥ

አዘርባጃን  አገር በሚገኝ ባኩ በተባለ ቦታ አንድ ግለሰብ ተጥሎ የተገኘ ባለቤት አልባ ቁስ በኪሱ በመክተት ሲጓዝ  በጉዞው ላይ ያሉትን በርካታ መንገደኞች ለከፍተኛ ጨረራ እንዲጋለጡ ያደረገ ሲሆን ከፍተኛ መቃጠልና ጉዳት የደረሰባቸው  5 ሰዎች ሲሞቱ አንዱ ለከፍተኛ የጨረራ ህመም (Rdiation sickness) ሲዳረግ 12 ሰዎች ደግሞ ለጨረራ ተጋልጠዋል፡፡ በኪሱ ከትቶ የተገኘውም ሲዝየም 137  (Cs-137) የተባለ ቁስ ነበር፡፡

ጨረራ አመንጭ ቁሶች በሚጓጓዙበት ወቅት ሌላውን ህብረተሰብ አላግባብ ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ምን ያህል ያውቃሉ?

        3ኛ

ቀን፡-  እ.ኤ.አ. ከመስከረም 12 -29 ቀን 1987

ቦታ፡-  ጉያና ጉያስ  (ብራዚል)

ክስተቱ፡-  የተበተነ የራዲቴራፒ ቁስ ያስከተለው ጦስ

ብራዚል  አገር በምትገኝ  ጉያና በምትባለው መንደር የሚገኝ አንድ የራዲዮቴራፒ ማዕከል በእርጅናና በብዙ አገልግሎት ምክንያት ከማደስ ይልቅ ወደሌላ አዲስ ቦታ ህንጻ በመስራት ሲቀይር ብዙ ዘመን የተጠቀመበትን ራዲዮቴራፒ መሳሪያ መነቃቀሉ በራሱ ጊዜና ወጭ የሚጠይቅ በመሆኑ እዚያው ትቶት ይሄዳል፡፡ አሮጌውን ህንጻ ሲያፈራርሱ ሌሎች ሰዎች እዚያ ፍርስራሾች ውስጥ የተተወ አሮጌ መሳሪያ  ሁለት ሰዎች ነቃቅለውት ከውስጡ ያገኙትን ቁስ ያወጡትና ወደ አንደኛው ቤት ይወስዱታል፡፡

በማግስቱም መስከረም 13 ቀን ሁለቱም ሰዎች ባሉበት ያስታውካቸዋል፡፡ አንደኛው ህክምና ቦታ ሄዶ እረፍት እንዲወስድ ተደረገ፡፡ ሁለተኛው መስከረም 18 ቀን ቁሱን ከቤት ውጭ አድርጎ ይከፍተዋል፡፡ ሌላውን አካል ለብረታብረት ሰብሳቢዎች ይሸጥላቸዋል፡፡ ብረታብረት ገዥውም ማታ ላይ ከገዛው ብረት መያዣ መሰል ውስጥ ሰማያዊ መሰል ብርሀን ሲወጣ ያይና ባለቤቱን ጠርቶ አብረው ያዩታል፡፡ ያካባቢያቸውን ሰዎችም ጠርተው እንዲያዩም ይጋብዙዋቸዋል፡፡ መስከረም 21 ቀን ሰዎቹ ብርሀን አመንጭውን ቁስ ተከፋፍለው ይወስዳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሰውነታቸው ላይ ይበትናሉ፡፡ ሌሎቹ ግን ወደ ቤታቸው ወሰዱ፡፡

ከዚያስ…..ይቀጥላል!

------------------------------------------------------------------------------------------------------

ወይ ጨረራ!

ለመሆኑ ጨረራን ምን ያህል ያውቁታል?

የፅሁፉ አቅራቢ፡ ታደለ ነ.(ኢጨመባ)

ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ እና በተከታታይ ክፎሎች የሚቀርብ

ክፍል - 1

በኢራን ላይ እንደነበረው ሁኔታ ዛሬ ደግሞ የሀያላኑ ፍጥጫ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ቀጥሏል፡፡ እስካሁን ግን ሀያላኑም የኢኮኖሚ ማዕቀብ ከመጣል እና ጆሮ ካሰለቸ ዛቻ የዘለለ አንዳችም የኮሪያን የኒውክሌር አረር ተሸካሚ የማስወንጨፍ ሙከራዋን ሊያስቆም ወይም ሊገታ የሚችል እርምጃ ሲወስዱ አልታየም፡፡ ጉዳዩ የኒውክሌር መሳሪያ ነዋ! ብትተኩስባቸው አጸፋውን ሊወስዱ ቢተኩሱባትም የጥፋት አረሯን ልትለቅ! ማን ዝም ብሎ ያልቃል?! በመጠባባቅ ተፋጦ በቃላት ጦርነት ብቻ መሰንበት፡፡ ዋናው ጉዳይ ቃታውን ማን ይሳበው? ነው፡፡ ቃታው የተሳበ ቀን ግን ዓለም ያኔ ወዮላት!

ማን ያውቃል? የሰው ልጅ ይኖርባትና ይበዛባት ዘንድ ፈጣሪ የሰጠውን ምድር ላንዴ እና ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ ይሰናበታት ይሆናል፡፡         

ለመሆኑ የኑክሌር የጦር መሳሪያ በእጅጉ ጅምላ ጨራሽ ከሚባሉት አደገኛ መሳሪያዎች ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ እንዲይዝና ዓለምን በቅጽበት ለማውደም እንዲችል ሀይል የሆነው ምን ይሆን?

 መልሱ ጨረራ(Radiation) ነው፡፡ አዎ ጨረራ!!!

ለመሆኑ ጨረራ ምንድን ነው?

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በዚህ አምድ በተከታታይ በሚቀርቡ ፅሁፎች የጨረራ አመንጭ መሳሪያዎችና ቁሶች እንዲሁም ኒውክሌር ቁሶች በተለያየ የዓለም ክፍሎች ካስከተሉት ጥፋቶች ውስጥ ለማስተማሪያነት ይሆናሉ ያላቸውን ዋና ዋናዎቹን በምሳሌነት በማቅረብ የጨረራን አፈጣጠር፣ የጨረራን ባህርያት፣ ጨረራ ለሰው ልጅ ስለሚሰጠው አገልግሎት፣ ጨረራ ባግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ ስለሚያስከትለው ጦስ፣ መወሰድ ስለሚገባው የጥንቃቄ እርምጃዎች፣ የሀገራችንስ ህዝብ ስለጨረራ ያለው ግንዛቤ እስከምን ድረስ እንደሆነ፣ ሀገራችንስ ጨረራ ሊያስከትለው የሚችለውን ችግር ለመከላከል በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች? ለሚከሰት የጨረራ አደጋ ፈጣን ምላሽ የመስጠት ዝግጁነት ምን ይመስላል? የመሳሰሉትን መሰረታዊ ዕውቀት ለወገኖቹ ሊያካፍል ይወዳል፡፡

በቀጣይ ክፍልም ከጨረራ ጋር በተገናኘ ሁኔታ በተለያዩ ሀገራት ውስጥ የደረሱ ዋና ዋና ጉዳቶች ይቀርባሉ፡፡

 ይጠብቁ!