Back

በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች አዳዲስ የማዕድን ሃብቶች መገኘታቸው ተገለፀ

በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች አዳዲስ የማዕድን ሃብቶች መገኘታቸው ተገለፀ
***************************************************************
የኢትዮጵያ ጂዮሎጂካል ሰርቬ ከሰሞኑ ይፋ እንዳደረገው የበጀት ዓመቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉት አስራ አንድ ወራት በተሰሩ የተለያዩ የምርምር ስራዎች በሶስት የሃገሪቱ ክፍሎች 18 የሚጠጉ የማዕድን ሃብቶች መገኘታቸውን አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ እንደጠቀሰው እነዚህ በማዕድን የበለፀጉ 18 ቦታዎች በአማራ፣ በትግራይ እንዲሁም በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የተገኙ ሲሆን መረጃቸውም 4000 በሚሆኑ የተለያዩ መስፈርቶች ተደራጅቶ ለኢንዱስትሪዎች፣ ለተመራማሪዎች እና ለባለሃብቶች መሰራጨታቸውን አስታውቋል፡፡

በማዕድን የበለፀጉት ቦታዎች በቁጥር ተከፋፍለው ሲቀመጡ የአማራ ክልል በብረት እና ሌሎች ማዕድናት የበለፀጉ ሰባት ቦታዎችን ሲያስመዘግብ፣ የትግራይ ከልል ደግሞ ወርቅን ጨምሮ ሌሎች ማዕድናት የሚገኙበትን ስድስት ቦታዎች ማስመዝገቡ ተነግሯል፡፡ በሌላ በኩል የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በከበሩ ድንጋይ እና ለሌች ማዕድናት የበለፀጉ አምስት ቦታዎችን አስመዝግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ጂዮሎጂካል ሰርቬ ይህን ግኝት ይፋ ባደረገበት ጊዜ በጉዳዩ ላይ ሃሳበቸውን ያካፈሉት የተቋሙ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ ታምሩ መርሻ እንደገለፁት ኢትዮጵያ አሁን ካሉባት አንገብጋቢ ችግሮች መካከል የስራ አጥ ቁጥር መጨመር አንዱ እና ዋነኛው ከመሆኑ አንፃር እንደዚህ ያሉ አዳዲስ የስራ መፍጠሪያ መንገዶች መገኘታቸው የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በመጠኑም ቢሆን ለማነቃቃት እንደሚግዝ ተናግረዋል፡፡ ሃላፊው ጨምረው እንደገለፁት የማዕድን ማውጣት ስራ ከሃገር ውስጥ ባለሀብት ወጪ የሌሎች ሃገራት ኢንቨስተሮችን ለማሳብ ሌላኛው መንገድ በመሆኑ ምርምሩን ይበልጥ በማጠናከር ሌሎች ቦታዎችን ለማግኘት ተቋሙ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁን ሰዓት የማዕድን ማውጣት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ከ135 በላይ ድርጅቶችና ኩባንያዎች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 80 ያህሉ ብቻ ህጋዊ ፍቃድ ኖሯቸው በዘርፉ እንደሚንቀሳቀሱ በቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ምንጭ፡ New Business Ethiopia እና Ethiopian Herald